ድንጋይ ብቻ አይደለም፣ አይደል ብረት ብቻ
መስዋእት እና ፅናት፣ የእምቢ ባይነት ዘመቻ
የአዲስ ዘመን ብስራት የእድገትሽ መባቻ
ላሊበላ አክሱም ነው፣ የዘላለም ሃውልት
የትውልድ አሻራ፣ የጽናት ምልክት
ኢትዮጵያ ሆይ፣ አንደአያቶቻችን ቆመናል ልጆችሽ
በደምና በአጥንት፣ በእንባ ሙሉ አይኖችሽ
ጉባ ላይ ተተክሎ፣ ወጋገን አርግዞ
ጭለማሽን ሊገፍ፣ ንጋት ጮራ ይዞ
የመከራሽ ዘመን፣ የተጫነሽ ድንጋይ
በልጆችሽ መስዋአት ሊወገድ ካንቺ ላይ
አባይ ሚተኛበት፣ ማደሪያ አግኝቶ ዜማ እያፈሰሰ፣
ወርቅ አፈርሽ ደልቶት፣ ምድርሽን በብርሃን አያረሰረሰ
ኢትዮጵያ ሆይ፣ አንዳያቶቻችን ቆመናል ልጆችሽ
በደምና በአጥንት፣ በእንባ ሙሉ አይኖችሽ
ድንበር ላይ ተተክሎ፣ ብርሃን አርግዞ
ጨለማሽን ሊገፍ፣ ንጋት ጮራ ይዞ
ሕዳሴሽ ንጋት ነው ብርሃን የነፃነት
ዳግማዊ አድዋችን፣ ምልክት የአንድነት።
ስመኘው ከመለስ፣ ክፍሌ ከአብቹ አብሮ
በትውልድ ቅብብል ስለሺ ከታዬ መክሮ
ያደመብሽን ዓለም አንደ ቀትር ጉም አባሮ ጨለማሽ ወዲያ ተገፎ ሰማይሽ ጠርቶ ከድሮ
ታሪክ ከሰራው ትውልድ ጋር፣ ግድቡ የእኔ ነው፣
እላለሁ ዘንድሮ አላለሁ ዘንድሮ!!!