ማስተዋልን ገንዘብ እናድርግ
ፖለቲከኞቻችን ዕድሜያቸው ቢያረጅም ፣ ከኩተት አስከ ሽበት ቢገረጅፉም ያንኑ የቀረና ሴራ ይዘው ብቅ ይላሉ።
እድሜ አያስተምራቸውም። ያንኑ የሞተ ፈረሳቸውን እየጋለቡ ወደ ስልጣን ተራራ ይቋምጣሉ።
በእነርሱ ምክንያት ለጠፋው የወጣት ሕይወት ፣ የወደመው ንብረት የእርሱ ድርሻ የላቸውም ?
አዛውንቶቹ እስከበደላቸው ወደ መቃብር ሲወርዱ < ኑ ወደ ገሃነም አብረን እንውረድ > ይሉናል።
እድሜያቸውን ጨርሰው ጅምር እድሜ ያላቸው ወጣቶችን ይዘው መቀመቅ ሊወርዱ ይመኛሉ።
በሌላ በኩል ወጣት ፖለቲከኞቻችን ከአዛውንቶቹ ስህተት ሳይማሩ ያንኑ ይደግማሉ።
ተስፋ የጨለመበትን ወጣት እያበሳጩ ወደ እቶን እሳት ይመግዳሉ።
ታዋቂነትና ዝናን ማግኘት እንጂ የወገናቸው መከራ አያሳስባቸውም ፣ የስልጣን ናፍቆት እንጂ የሞራል እዳ የለባቸውም ፣መብት እንጂ ግዴታ እና ሀላፊነት ያለባቸው አይመስሉም።
በዚህም #ያልተማሩ የሚባሉት የሰሯትን ትልቅ ሀገራችንን #ተማርን የሚሉት አፈራርሰው ትንንሽ ካላደረግን እያሉ ይራኮታሉ።
እኛም ህብረተሰብ የምንባለው ከታሪክ የምንማር አልሆንም። ለምን? እንዴት? መቸ? እና የት? የሚል ጥያቄ አንጠይቅም።
በስሜት እንቃወማለን፣ በጭፍን እንደግፋለን፣ ተሰለፍ ሲባል መሰለፍ እና መንጋጋት ነው።
ለተቃውሟችን ምክንያት የለን፣ ለድጋፋችን ለከት የለን፣ ያገኘ የሚጋልበን ሌጣ ፈረስ፣ ሀሉም የሚጭነን የሕዳር አህያ ሆነናል።
ትናንት ብልጣብልጦች ያደረሱብንን ረስተን ዘመነኞችን ያለ ጥያቄ እየተቀበለን አበሳችንን እናያለን።
ትናንት ማን ነበርክ ? ነገስ ምን ልትሆንብኝ አስበሃል? ብለን አንጠይቅም።
ምንም ማንም ብትሆን ድምፄን እንጂ ሕይወቴን አልሰጥህም አንልም።
ከታሪክ መማር አልቻልንም። ሆኖም ከታሪክ መማርን መማር ይገባናል።